ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Transforming manufacturing from trend to culture!

ወ/ሮ የመንዝወርቅ ግረፌ ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት በ2016 በጀት ዓመት 1ሺህ 565 አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በሊዝ ፋይናንስና በስራ መስኬጃ ብድር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የፕሮጀክቱ አሰተባባሪ ወ/ሮ የመንዝወርቅ ግረፌ ተናገሩ።

ከዓለም ባንክ በተገኘው የብድር ድጋፍ ከ106 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረጉንና በዚህም ፕሮጀክቱ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን አሰተባባሪዋ አብራርተዋል።

ወ/ሮ የመንዝወርቅ አክለውም ኢንተርፕራይዞች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር አቅዶ ባከናወናቸው ስራዎች 221,367 እንደ ሰብል፣ ከብቶች፣ ፍየሎች፣ በጎችና ግመሎች የመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ያስመዘገቡ ከ97 ሺህ በላይ የብድር ጥያቄ አቅራቢዎች በባንኮች በመስተናገድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በፕሮጀክቱ ዕቅዶች አፈጻፀም ድርሻ ላላቸው የተለያዩ ተቋማት ከ30 በላይ የዕቃና የአገልግሎት ግዥዎች ለመፈጸም የሚያስችሉ የኮንትራት ውሎችን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመፈጸም ወደትግበራ ተገብቷልም ብለዋል።

በአገር ውስጥ ያሉ አነስተኛና መካካለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች መራጃ ማሰባስብ ስራን ለማከናወን ከአትዮጵያ ሰታትስቲክስ አገልግሎት ጋር ተዋውሎ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት የፕሮጀክት አስተባባሪዋ በጦርነት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ የየክልል የዘርፉ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን አቅም ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች በንግድ ልማት አገልግሎት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ በ2017 በጀት ዓመት ለ400 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስልጠና ድጋፍ ለመስጠት ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ቅጥር በመፈፀም ወደስራ መግባቱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ሮ የመንዝወርቅ ገልፀዋል፡፡

News