ስለ እኛ

አምራች ኢንተርፕራይዞችን ማጠናከር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሽግግርና ማህበራዊ ብልፅግና !

ስለኛ

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአምራች ኢንተርፕራይዝ ልማት በሐገር ዓቀፍ ደረጃ በላይነት እንዲመራና ዘርፉ በሐገራዊው ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል በ1934 ዓ.ም የተቋቋመ አንጋፋና ታሪካዊ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ በእነዚህ ከ80 በላይ በዘለቁ ዓመታት ዘመናዊ ሐገራዊ የአምራችነትና የንግድ አስተሳሰብን በመፍጠርና በማስፋፋት፣ በሐገራችን “የመጀመርያ” የሆኑ ከሐገር በቀል የእደ ጥበብ ስራ ውጤቶች እስከ ዘመናዊ ማምረቻ ማሽኖች የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ በማድረግና በርካታ ሐገራዊ ባለሐብቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ በተለይም አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ልማትን እንዲደግፍ ተልዕኮውን ለመወጣትም የክልሎች፣ ከተማ መስተዳድሮችንና የባለድርሻ አካላትን አቅም በማስተባበር አምራች ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የስልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የግብዓትና  የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ከማድረግም ባሻገር የማምረቻና የምርት መሸጫ ቦታዎች እንዲለሙላቸው፣ መሠረተ ልማትም እንዲሟሉላቸው ያደርጋል፡፡

የቢዝነስ ከባቢውን ምቹ ለማድረግና ድጋፎች ወጥ በሆነ አግባብ መሠጠት እንዲችሉ ልዩ ልዩ ፖሊሲና ስተራቴጂዎች፤ ደንቦች፤ መመሪያዎች፤ የድጋፍና የአሠራር ማዕቀፎች፣ ያዘጋጃል፤ እንዲኖሩና እንዲሻሻሉ ልዩ ልዩ ድጋፍ ይሠጣል፡፡

በሐገራችን እስከ ሠኔ 2016 ዓ፤ም ድረስ በ26,862 ስራ ፈጣሪዎች የተመሰረቱ ከ12,751 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 8,574 ያህሉ አነስተኛ አምራቾች ሲሆኑ 4,177 ያህሉ ደግሞ መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡

እነዚህ አምራች ኢንተርፕራይዞች በየዓመቱ በአማካኝ በወጪ ንግድ ከ33 ሚልየን ዶላር በላይ እያስገኙ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ 2 ቢልየን ዶላር የሚገመት ገቢ ምርትን በመተካት በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

 

የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት

የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መደላድል ላይ ለማስቀመጥና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ዕውን ለማድረግ የአምራች ኢንተርፕራይዝ ልማትን ማስፋት ወሳኝ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ተቋማችን አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በብዛት እንዲፈጠሩ፣ እንዲጠናከሩና እንዲሸጋገሩ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ጥረቶችም አምራች ዘርፉ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂና በማምረቻ ቦታ አቅርቦት፣ በግብዓትና ገበያ ትስስር፣ በስልጠና፣ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና በንግድ ልማት አገልግሎትን በመሳሰሉ ድጋፎች እንዲጠናከር በማድረግ ለዘርፉ ልማት አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ እንገኛለን፡፡
እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በወጥነት ለማስፈፀም እንዲቻልም ልዩ ልዩ የድጋፍና የአሠራር ማእቀፎችን፣ መመሪያና ደንቦችን በማዘጋጀትና መዋቅሩን በልዩ ልዩ አግባብ በማጠናከር የዘርፉ ልማት በውጤታማነት እንዲከናወን በማድረግ ጠንካራ የአምራች ዘርፍ ልማት ለመፍጠር ችለናል፡፡
እነዚህን ውጤቶች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የጀመርናቸውን ጥረቶች ለማሳካትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዲችል በአክብሮት እንጠይቃለን!

አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር

ዓላማዎች

•አምራች ኢንተርፕራይዞች እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ በማድረግ በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ፣ እንዲሁም ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት መሠረት መጣል፤

•አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ-ልማቶችን በማልማትና በማስተዳደር ዘርፉ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ድጋፍ መስጠት

ተልእኮ

ዋናው ተልዕኮ ለአምራች አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲሆን የዘርፉን ወሳኝ ባለድርሻ አካላት አቅም መገንባት፣ መሠረተ ልማቶች እንዲለሙ ማድረግ፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብርን በማሳደግ የዘርፉን መስፋፋት፣ መጠናከርና ተወዳዳሪነት ማሳደግ ነው።

ራዕይ

“የአነስተኛና መካከለኛ ማፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ”

የልማቱ ሥልጣንና ተግባር

ልማቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

፩/ የኢንተርፕራዝ ልማትንና ሽግግርን ለማፋጠን የሚረዱ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች እንዲወጡ ሐሳብ ለሚኒስቴሩ ያቀርባል፤ ተዘጋጅቶ ሲጸድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፤ 

፪/ የኢንተርፕራይዝ ልማቱን የሚደግፉ የድጋፍ ማዕቀፎችን፣ የአሰራር ስርዓቶችን እና እቅዶችን ያዘጋጃል፤ ይተገብራል፤ ተግባራዊ እንዲሆኑም ያስተባብራል፤ 

፫/ ለኢንተርፕራይዞች በተለይም ገቢ ምርቶችን ለሚተኩ እና ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች በጥናት እንዲለዩና መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋል፤

፬/ ዜጎች በኢንተርፕራይዝ ልማት እንዲሰማሩ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ሥራ ይሠራል፣ የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ አቋቁመው ወደ ስራ እንዲገቡ ከሚመለከታው አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፤ 

፭/ የኢንተርፕራይዝ ልማቱን የሚደግፉና የሚያስተባብሩ የክልል ተቋማትን፣ የባለድርሻ አካላትን፣ የልማቱን ሰራተኞችና የዘርፍ ማኅበራትን የማስፈፀም አቅም ይገነባል፤የአቅም ግንባታ ሥራ ከሚሠሩ ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሠራል፤

፮/ ለኢንተርፕራይዞች አስፈላጊ የሆኑ የሥልጠና፣ የጥናት፣ የፋይናስ፣ የማምረቻ መሣሪያ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምክር አገልግሎት፣ የማምረቻ ቦታና መሠረተ-ልማት፣ የግብዓት፣ የገበያ ትስስርና ሌሎች ድጋፎች በክፍተትና በዕድገት ደረጃ ላይ ተመስርተው እንዲቀርቡ ያደርጋል፤ ይደግፋል፣ ያስተባብራል፤ 

፯/ ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር የኢንተርፕራይዞችን ልማትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ይሠጣል፣ እንዲያገኙ ያደርጋል፣ ያስተባብራል፤ 

፰/ የኢንተርፕራይዝ ልማትን ሊያፋጥኑና ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ይለያል፣ ይቀምራል፣ እንዲሰፉ ያደርጋል፤ 

፱/ ለኢንተርፕራይዞች ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክት ፕሮፋይሎች፣ ሞዴል ቢዝነስ ፕላኖችና ስፔሲፊኬሽኖች ያዘጋጃል፣ ለተጠቃሚዎች ያሰራጫል፤ 

፲/ በልማቱ ሥር የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ለኢንተርፕራይዞች እና በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ዜጎች ሥልጠና ይሠጣል፣ እንዲሠጥ ያደርጋል፣ መለዋወጫዎችንና ችግር ፈች የሆኑ የምርትና የቴክኖሎጂ ናሙናዎችን ያዘጋጃል፣ በስልጠና ያሸጋግራል፤ የፈጠራ ሃሳብ ይዘው ለሚመጡ ዜጎች ሃሳባቸውን ወደ ተጨባጭ ምርት እንዲለውጡ ያደርጋል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፤ 

፲፩/ የኢንተርፕራይዞች የቁጠባ ባህል እንዲያድግና የሥራ ማስኬጃና የማምረቻ መሳሪያ ፋይናንስ ከአበዳሪና ከአከራይ ተቋማት እንዲያገኙ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፤ ከሚመለከተው አካል ጋር በመተባበር ምቹ የፋይናንስ አቅርቦት ስርዓት ይዘረጋል፤ 

፲፪/ ለኢንተርፕራይዝ አገልግሎት የሚውሉ መሠረተ-ልማት የተሟላላቸው የማምረቻ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከላት ያለማል፣ ያስተዳድራል፤ 

፲፫/ ኢንተርፕራይዞች እርስ በእርስና ከከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣ ከሌሎች ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በግብዓት፣ በገበያና በቴክኖሎጂ የሚተሳሰሩበትን ይቀይሳል፣ ተግባራዊ ያደርጋል፤ ስልቶችን 

፲፬/ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወርሃዊ፣ ክልላዊ፣ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አውደ-ርዕይ ያዘጋጃል፤ ክልሎች እና የግል ተቋማት በተናጠልና በጋራ እንዲያዘጋጁ ያመቻቻል፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ላይ ኢንተርፕራይዞች እንዲሳተፉ ያደርጋል፤ይደግፋል፤ 

፲፭/ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪ ለማድረግና ዜጎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በጥናት ላይ የተመሠረተ የማበረታቻ ስርዓት እንዲዘረጋ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ ይሰራል፤ ተፈጻሚነቱን ያረጋግጣል፤ 

፲፮/ ለኢንተርፕራይዞች የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት እንዲቋቋሙና ወደ ሥራ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ይሠራል፤

፲፯/ በኢንተርፕራይዝ የሚመረቱና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ደረጃ እንዲወጣላችውና የወጣላቸውም የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ 

፲፰/ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ተመሳሳይ አላማ ካላቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የትብብር ስምምነት ያደርጋል፣ ተፈጻሚ እንዲሆንም ይሰራል፤ 

፲፱/ ለዘርፉ ልማት አጋዥ የሆኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች እንዲለሙ ያደርጋል፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መረጃዎችን ያደራጃል፣ ይተነትናል፣ ያሰራጫል፤ 

፳/ ኢንተርፕራይዞች በአካባቢ ጥበቃ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ድጋፍ ያደርጋል፣ ይከታተላል፤ 

፳፩/ ልማቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣው ደንብ መሰረት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ክፍያ ያስከፍላል፤ 

፳፪/ የጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ልማትና ሽግግር በተመለከተ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የድጋፍ ስራ ይሠራል፣ አስፈላጊውን አሰራሮች ይዘረጋል፤ 

፳፫/ የንብረት ባለቤት ይሆናል፤ ውል ይዋዋላል፤ በስሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 

፳፬/ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ያከናውናል፡፡